አላሸንፍህም
አላሸንፍህም
እፋለምሃለው እታገልሃለው እፋተግሃለው
ጎኔ እስኪቆስል
ሸካራው አካሌ ላንተ እስኪለሰልስ
ጉጠቴ እስኪለቅ
በጎን ያበቀልኩት ስታቀፍ የወጋህ
ካ’ካሌ ተሰብሮ ከላዬ እስኪወድቅ
እተሻሽሃለው
ትዕቢት ወጥሮት
መሬት በግንባሩ ቆፍሮ ቆፍሮ
አፈሩን ባ’ናቱ እንደሚነሰንስ
ገጣሚ ፈልጎ ቀዬ እንደሚረቢሽ
እንደ አበያ በሬ
ጉልበት እንደሞላው እንዳልተጠመደ
እንደ ጎበዝ ወይፈን
ቀንበር አልይዝ ብዬ አስቸግርሃለው
ደሞ አጎነብስና ውግያ እገጥማለሁ
አንተኑ ወግቼ ካንተ ላይ ቦጭቄ አንተን በአናቴ እስክነሰንስህ
እታገልሃለው እፋለምሃለው ባላሸንፍህም እፋተግሃለው
፠፠፠፠፠፠፠፠≤≥፠፠፠፠፠፠፠፠
ትናጋውን ይዞት ህቅ እንቅ እንዳለው
እንባ እንደጠመቀው
ትዕቢት እንደሞላው እንደጨቅላ ጩጬ
ታላቁ ጋር ገጥሞ እንደሚለፋደድ
ሰንዝሮ ሲማታ አየር እንደሚዝቅ
ኢላማ እንደሳተ እንደሚዘባርቅ
ተነስቶ እንደሚወድቅ መቆም እንደማይችል
እንደተላላጠ አደጋ እንዳገኘው
ሰውነቱ ደቆ አካሉ ተላቆ
መቆም እንደማይችል ምርኩዝ ተደግፎ
መሮጥ እንደማይችል ተዘርሮ ወድቆ
መነሳት እንዳይችል እንደተሰበረ
መረታቱን አምኖ እንዳቀረቀረ
መሣሪያ እንደሌለው እጁ እንደማየሠራ
ከበው እንደያዙት ብቸኛ ወታደር
እንዲያ እስክሆን
ድረስ
እንዲያ እስክሆን
ድረስ እታገልሃለው።
እፋለምሃለው።
መቆም እንዳልቻለ
ራሱን እንደሳተ
ኃሳቡን ለመግለጽ
እንደሚንተባተብ
እንደተለጎመ ቃላት
እንደጠፋው
እንዲያ እስክሆን
ድረስ
ባላሸንፍህም እታገልሃለው
እታገልሃለው
እፋለምሃለው።
ቃልህ እንደሰደፍ
ጎኔን አንቆራጦ
መተንፈሻ አጥቼ እስክታመም
ድረስ
መቆም እስከማልችል
አካሌ ተሠብሮ
ቅልጥሜ ተላቆ ሲቃ እስከሚሰማኝ
ቁስሌ መርቅዞ አካሌ
እስኪተላ
ገምቼ ሸትቼ ራሴን
እስክጠላ
ባላሸንፍህም እታገልሃለው
እፋለምሃለው
ምክንያቱም በዚያ ውስጥ
አንተ በሠበርከኝ
በስብራቶቼ
መርቅዘው በቆሙት
በጠባሳዎቼ
ፍቅርህን አያለው
ደግሞ ጭካኔህን
ጠገግ እያገኘሁ ትናንትን
ማለፌን
ሰብረህ ማባበልህ
ቅልጥሜን መግጠምህ
ቁስሌን መፈወስህ
ቀንዴን መቀየርህ
ቢያስገርመኝም
ቢያስደንቀኝም
እኔ ግን አሁንም
ህመምን መምረጤ በራሱ
ቢያምም
ያልተሠራ አካሌ ተሠርቶ
እስክፈፀም
ትግሌን አላቆምም
ባላሸንፍህም።
በ፳፬-፪-፪፻፻፲፩ ተጻፈ።

Comments
Post a Comment