እንገንጠል

 

በአንድ ወቅት በዓዲግራት ከተማ በማገለግልበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየሳምንቱ የተለያዩ ድራማዎች እንሰራ ነjበር። በእኒህ ወቅት ስንቅር ብለው ከቀሩልኝ ድራማዎች መካከል የአካል ግንድ በመሆን የሰራሁት ድራማ ዋነኛው ነው። የዚህ ድራማ ጭብጥ አካላት ሁሉ የተሠኩበት የአካላቱ ግንድ በድንገት ጥያቄ ይቀርብለታል። የእንገንጠል ጥያቄ። የአካሉም ግንድ ጥያቄአቸውን በሠማ ጊዜ በእጅግ ይደነግጥና ምላሽ መስጠት ይጀምራል። ምላሹንም “ለምን?” በሚል ጥያቄ ይመልሳል። አካላቱም አንድ በአንድ እየተነሱ መመለስ ይጀምራሉ። እኔም ትንሽ እርማት ጨምሬበት አቅርቤዋለሁ።
ከተናጋሪ አካላቱ መካከል አንዷ ምላስ ነበረች። “እኔ እኮ  አይጣል። አይጣል ያለኝ ተሰጥኦ። ስንቱን ግብግብ እንዳረኩ። ቅመሺ ስትለኝ ስቀምስ። ተናገሪ ስትለኝ ስቀምስ። ከአፍ የሚወጣ ጂ ወደ አፍ የሚገባ ጣጣ የለውም። አያረክስም! እየተባባልን። ያልተጋትኩት የለም። ደሞ እንደአንዳንዶች እንኳ የሚደረግ ጥቅማ ጥቅም የለኝ። ባለፈው ምን ሰማሁ። የአካል ግንድ ምላሱን ለመንከባከብ በየወሩ አዳዲስ ለስላሳ ብሩሾች ከነፈሳሽ ሳሙናው በጅቷል የሚባል ነገር ደረሰኝ። ዶሮን ሲያታሏት አሉ። እንደው አሁን ማን ይሙት ይህ እሙን ነው። ትላለህ? ጆሮህን ፈልግ ብትለኝ እንኳ እኔ አልሠማህም። ጥርስ እያማረበት በሆነው ባልሆነው ሲገጥ እኔ  እርሱ በታጠበበት ውሃ  የስንቱን ነገር ጣዕም እናዳጣሁ አንተ የማይገባህ የኔ ብቻ ችግር ነው። እናም ወስኛለው። ከእንግዲህ በእንዲህ አይነት ጭቆና መቆየት መሰንበት አልፈልግም፤ ለየኝ ድርሻዬ ስጠኝና ልሂድ።” አለች።
 “የአካል ግንድ ሆይ? እኔ አድርግ ሂድ ወዳልከኝ ሁሉ ይህ ጭቃ ነው። ይህ እሾህ ነው። ይህ ድንጋይ፣ ኩርንችት፣ እንቅፋት ነው። ሳልል አንተ እንደወደድከኝና እንደወደድከው ሄጃለው። ደግሞም እሩጫለው። አሁን ግን በቃኝ እራሴን መቻል እፈልጋለው። ማንነቴ እኮ ላወቀበት ትልቅ ጥቅም አለው። አንተ የወደድከውን ሳይሆን እኔ የወደድኩትን መርገጥ እፈልጋለው። ባጭሩ ለመናገር ያህል ከአንተ ያገኘሁት ነገር ቢኖር ዘንጌን የሚሸፍን ብጣቂ ጨርቅና  ላንተው ጥቅም ብለህ ያለበስከኝ ጫማ ብቻ ነው። ስለዚህ ከጓደኞቼ አይን፣ ጆሮ፣ እጅና  ምላስ ጋር አውግተናል። ሁላችንም በየፊናችን የራሳችንን ኑሮ መኖር አስበናል።” አለ። ሌሎችም ፉከራ እንደሚቀበል ጎረምሳ በዝምታ ውስጥ በፊታቸው በሚታይ መልዕክት እሰይ አሹ አሉ። 
የአካል ግንዱም “ሌሎቻችሁስ?” ሲል ”እኔም በበኩሌ ካንተ ጋር ብዙ ተጣበኩ። የምትበላውን አጎረስኩህ ያሰብከውን ከወንኩልህ። ነገር ግን እኔን ለማታለል ካሰርክልኝ ሰዓትና ሌሎች ቅራቅንቦ በስተከር አንዳች የኔ ምለው የለኝም። ስለዚህ እኔም ልክ እንደ እግር የራሴን ኑሮ  መኖር እፈልጋለሁ። ሠርቼ  ማጌጥ አምሮኛል ከማንም እሄዳለው ባይ የተሻለ  ብቃትና  አቅም እንዳለኝ ይታወቃል። ስለዚህ እኔም ተገንጥዬ መለየት እፈልጋለው“ አለ።
“እኔም ያላየሁትን ማየት፣ ማድነቅ፣ መደመም እፈልጋለው። ላንተ ያልሆንኩት የለም ታውቃለህ። ብዙ አይቼልሃለው። በጢሱ፣ በአቧራው፣ በብርሃኑ፣ ደግሞ  በድንግዝግዙ ያልሆንኩልህ የለም። አንተ  ግን አፍንጫን ተደግፎ  ፊቴ ከተደነቀረው መነጽር ከሚሉት ነገር ውጪ ምንም አልፈየድክልኝም። ስለዚህ መገንጠል እፈልጋለሁ።” አለ ዓይንም። 
  “እንግዲህ ለመስማት ሳልዘገይ ታንቡሬ እስኪነደል፤ አንዳንዴም የሹክሹክታን መልዕክት ለመለየት ስኮረኮር ትንሽ አሞኝ ጭው ያልኩ እንደሁ ከአፍ በምታመጣልኝ አንድ ጭብጥ ትንፋሽ ‘ቸር አሰማኝ’ እያልክ ትወተውተኝ ነበር። እንግዲ እቅሜን  ያህል ቸሩንም መርዶውንም አሰምቼሃለው። እንደው አንተኳ ጥሩ ነበርክ። ነገር ግን ከአንዳንድ ውርጋጥ ጋር መኖር ይከብዳል። እጅ ቆሻሻዬን በሚያጸዳበት ወቅት አጉል ከባባድ ህመም እየጨመረብኝ ነው። አይንም ቢሆን ይህንን አላይም ብሉ ለህመም ዳርጎኛል። እና እኔም አንተን እየወደድኩ ያለኝ አማራጭ መገንጠል ነው።” 
የአካል ግንድም ይህንን ከሰማ በኋላ  ምላሽ ሰጠ። “አንዳችን ያለ አንዳችን ምንም ነን።” ሳይቸርስ “ኤጭ ዲስኩር ተጀመረ። ይህአባባልነው።” አለች ምላስ ዝግ ባለ ድምጽ። ስለሰማት “በእርግጥ አባባል ነው። ግን ህልውና  ያለው አባባል ነው። አንዳችን ያለ አንዳችን ምንም ነን።’’ “ይደገም! ይደገም!” አሉ። የውስጥ አካላት። “አንዳችን ያለ አንዳችን ምንም ነን። አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል የሚባለው ምላስ ስለሌለ ሳይሆን የምላስ ምንጭ ራስ ወይም ጭንቅላት ስለሆነ ነው። ሁላችንም የራሳችን ውጤቶች ነን። እራስ ይመራል። እራስ የተሞላውን በእናንተ በኩል ይተፋል። ውድ አካላቶቼ የቀመስነው ምላስ ስላለን ሳይሆን ምላሳችን ከራሳችን ጋር ስለተሰካ ነው። እግርም፣ እጅም ዓይንና ጆሮም ቢሆን የሚሰሩትን የሚሰሩት ከራሳቸው ጋር ስለተሰኩ ነው። ራስ መሪ ነው ስለዚህ ዛሬ  ሁላችሁም ራሳችሁን ፈትሹ። 
ዓይን ማየት የቻለው ከራስ ጋር ስለተሰካ ብቻ አይደለም። ማየት የቻለው ብርሃን ስላለም ጭምር ነው። ዓይን ከራስ ጋር ምንም ያህል ሽርክ ቢሆኑ ያለብርሃን ምንም አይፈይዱም። ጆሮም ያለድምጽ፣ ድምጽ የመርገብገብ ውጤት ነው። ምላስ ሲርገበገብ ድምጽ ይፈጥራል። ጆሮም ይሠማዋል። 
እጅ የከወነውን ምላስ ያስራዳል። ምንም እንኳ ድርጊት ከምላስ በላይ ድምጽ ቢኖረውም። እርግጥ ነው እግር ላወቀበት ሀብቱ ነው። እግር ብቻ ግን አይደለም። ጆሮም፣ ዓይንም፣ እጅም፣ ምላስም ጭምር ሀብት ናቸው። 

አካሎቼ አካል አካልን ካልጠቀመ ተገንጥሎ፤  ህልውና እሲኪያጣ ያልታመመውን ህመም መታመም እንጂ ሌላ ምንም ረብ የለም። ስለዚህ አንገንጠል። እንደውም እጆቻችን የሌሎችን እጆች ይያዙ። አቅም ይጨምሩ። ያልተደመሩትን ይደምሩ። 
አካል ንግግሩን ሳይጨርስ ብዙዎቹ አካላቶች ተነስተው መጓዝ ጀመሩ። የአካል ግንድም መኮለታተፍ፣ መሽመድመድ፣ መታመም፣ መድማት እና  ሌሎች ስቃዮችን መሰቃየት ጀመረ። በስተመጨረሻም የአካል ግንድ እንዳልነበር ሆኖ ድባቅ እንደተመታ ተዘረረ።  በዚህ ወቅት ቀድሞም ድንዝዘው የነበሩት አካላት ሁሉ መታመማቸውን እና መገንጠላቸውን አመዛዝነው የመሰቃየት ደሥታ እየተጎነጩ ተጓዙ። ነገር ግን የሥቃዩንም ደሥታ ለመኖር ብዙ አልቆዩም። በውስጣቸው ከአካል ግንድ ተካፍለው ያዘሉት ደም አለቀ። በዚህ ወቅት ነበር ዓይን የአካል ግንድ መውደቁን አይታ የጮኸችው። እግርም ፈጥኖ  እጅን በመያዝ የተመለሱት። ሄደውም እግር ተሠካና  አቆመው። እጅም ተሰክታ  በዳበሳ አስደገፈችው። እጅና እግር ግን እንዲህ አሰቡ። እኒያ ሦስቱ አካላት አያስፈልጉንም። የችግር መንስኤ ሁሌም  ተመልካችና ሰሚ ናቸው። ደሞም ከምንም በላይ እኒህን ብንቀበል ምላስን በፍጹም የማይሆን ነገር ነው። በማለት ተስማሙ። እጅም ‘ያፍህ ቃል ወጥመድ ነው።’  የሚለውን “የምላስ ቃል ወጥመድ ነው” ብላ አመናፈሠችው። እሱም ብቻ አይደለም “ከምታዩትና ከምትሰሙት ተጠበቁ” ይል የለ። አለ እግር። እኛ ያመናቸውን ነገሮች ሁሉ ያመናቸው በሠማናቸውና ባየናቸው ነገሮች ነው። ስትል እጅ። እግር ይሄኔ ራራ ፥  “ባክሽ እኛም እኮ  ሄደን ነበር። ግን መጥተን ስንገጠም የአካል ግንድ ምንም አላለን። እድል እንስጣቸው።“ ተባባሉ። እድልም ተሰጣቸው። ያኔ  ለተወሰነ ወራት ያፈረሱትን ቅጥር መገንባት ላይ ትኩረት ስላደረጉ ከጊዚ ቦኋላ ነበር ያብሮነትን፣ የአንድነትን እና  የልዩነትን ጣዕም ማጣጣም የጀመሩት። 
“ወይ ልዩነት” አለች ምላስ!? “ምነው” አሏት። “ሁልሽም እንደኔ  ምላስ ብትሆኝ ምን ይውጥሽ ነበር?” አለቻቸው። ሁሉም ከልባቸው ሳቅን ለጥርስ ላኩለት። 
እንገንጠል የሁሉ ማስፈራራያ ሆናለች። ኮሾሮና  ከረሜላ  እየደለለው ያደገ ሁሉ። በድንገት ብድግ ይልና እንደጠፋው ልጅ ድርሻዬን ይላል። ከዛም እዚህ ነኝ ሳይል እልም ይላል። ይህን ስጽፍ አንድ ያባቴ አጎት ልጅ አያቴን ሁሌ እንዴት ያስቸግራትና ያማራት እንደ ነበር ትዝ አለኝ። እንደው ብድግ ይልና ሁለት ወይፈን ነድቶ  ይሸጥና በዛው የት ነህ ላይባል ድምጹን ያጠፋል። ይሄኔ አያቴ ወገቧን አሸርግዳ ልጄን ያየ ትገባለች። ሁሉ ሲያልቅ ደግሞ ይመለሳል። አሁንም ድንገት ሀገር ሰላም ሲሉ ጥጃ ነድቶ የሄዳል። በአንድ ወቅት ሄዶ። አያቴ ዕርሟን ካወጣች በኋላ የደንብ ልብሱን ለብሶ በድንገት ወታደር ሁኑ ከች ሲልላት የሠፈሩ ሚሊሻዎች የተኩስ እሩምታ ከፍተው እንኳን ደህና መጣህ ሲሉት፤ የሆነ ሂድ ሂድ ጀግን ጀግን የሚያሠኝ ነገር እንዳለው ገባኝ። እናም ከጊዜ በኋላ  በዛችው የገጠር ከተማ ሲኖር እንደው በድንገት ወጥቶ አደረ። ይኸው እስከዛሬ ድምጹ የለም። 
          የጠፋው ልጅ አካላቱ የዘውት እንደሄዱት ደም ድርሻዬን ሲል ልጁ በጊዜው መያዝ የሚችለውን ነበር ድርሻዬ ያለው። ምክንያቱም በዚያ ቤት ውስጥ ልጁ ድርሻ የለውም። ሁሉ ያ’ባቱ ነው። ያ’ባቱ ሁሉ ደሞ የልጁ ነው። ሁሉ የራሱ ሆኖ ግን ድርሻዬን ብሎ የወሰደው መያዝ የሚችለውን ብቻ ነው። እግዜር ይህ ልጅ ጠፍቶ እንዳይቀር ሲተነቀቅለት፤ እርያን አሳየው። እድሜ ለእርያ አንድ ቀን አነቃው። ተገንጥሎ  የገባበት ቦታ ባርነትን አከናነበው። የዚያ ሀገር ጌታ ከባርያዎቹ ይልቅ ሀብቶቹ ለሆኑት አሳማዎች የሚጠነቀቅ ሆነና ይህ ጠፊ የአሳማን ምግብ መንጠቅ አማረው። መለየት ላልተገዛንላቸው ነገሮች የመገዛት እድል ይፈጥራል። ምክንያቱም እራስን መከላከል እስኪሳነን ድረስ ብቸኛ ስለምንሆን። የመገንጠል ትርፉ ገበና ሸፋኝ ማጣት ነው። 
ዛሬ ዛሬ አንቀጽ 39ን ማንም ያውቃታል። የስነ-ዜጋና  ስነ-ምግባር መምህሩም ይህችን ሲያብራራ ሁሉን ያወቀ ያህል ይሠማዋል። እና ይህችን ማስፈራሪያ የሚያውቃት የታመመ ይመስለኝ ነበር። የተገነጠለም ሌላ መገንጠል ያምረዋል። ሚስት ባሏን ጥንቅር ብለህ ትቀራለኻ እኔና ልጆቼ እንደሁ እንኖራለን። ትልና ነፍስ ባልዘሩ ጨቅሎች ባሏን ከአባትነቱ ኑሮው ትገነጥለዋለች። ጎበዝ የዶሮ ብልት አስመሰለችው እኮ፤ እኔ የፍቺ ውጤት ነኝ። ሳስበው ይዘገንነኛል። አንዳንዱ ድል ባለ ሰርግ አግብቶ በወሩ፤ ወርም ከሠነበቱ ነው። ውይ ተለያዩ  እኮ ይባላል። ፍቅረኞች በትንሽ ነገር አውርተው እንደመስማማት እንዳዩትና እንደሠሙት ሴት እሷ ብቻ ያለች ይመስል ይልና ቀይ ካርድ ይመዝባታል። 
ሙስሊሙ፣ ኦርቶዶክሱ፣ ካቶሊኩ ጴንጤው ሁሉም እገነጠላለው የሚለው አለው። ኧረ ወዲያ። መገንጠልን ነበር ከሠው ልብ መገንጠል። ትንሽ የጴንጤው ወግ ውስጥ ስላለሁ አንዳንዱ እንገንጠል ባይ ያስቀኛል። እኛ ተጨቁነናል። እንገነጠላለን። ልጆቻችንን ስትጠሩ ሰምተናል ከዛሬ ጀምሮ  እግራች እኛ መንደር ይደርስና ይላል። ሌላኛውም ሌላ ነገር ይላል። 
          ሰው ጉልበት አግኝቶ  የተገነጠለ ገጽ ጽፎ  መጽሃፉን ሲያሟላ  ሌላው ደግሞ  ከስር ሌላ ገጽ ይቀዳል። ሌላው ተሳክቶለት የተቀደደ መሬት ሲሰፋ ሌላው ደግሞ  ሌላውን መሬት ለመቅደድ ይገዘግዛል። ምንም ይሁን ምንም ግን መገንጠል። በተለይ ከራስ እንደመገንል የሚያም የለም። አንገት ምስክሬ ነው። ከራስ የተገነጠለ የሞተ ነው። መጽሓፍ ሲናገር ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ። 1ቆሮ 11፡3 ከትዳሩ የተገነጠለ ሰው ኑሮ እጅግ ከባድ ነው። ከክርስቶስ የተለየ ማንነትም አንገትን በካራ እንደመቅላት ነው። ራስ የሌለው ህይወት ሙት ነው። ሰው ለሰው መኖር የሚጀምረው ራስ ሲኖረው ነው።  በህክምናው የሞተ አካል እንዲንቀሳቀስ ይደረጋል። አልያ ግን የተመረዘው ሙአቲነትን እንዳያስፋፋ ይቆረጣል። ራስ የሌለው ሁሉ ሙት ነው። ራስ አለኝ? ብሎ  መጠየቅ ደግሞ  ብልህነት ነው።
ራስ ካለን አካላችንን እንፈትሽ።
አበቃ።
በ፴-፫-፪፻፻፲፩ ተጻፈ።

Comments

Popular posts from this blog

ስንፍና

አላሸንፍህም